

ረዥሙ መተላለፊያ ላይ ድንግዝግዝ ባለ መልኩ ብርሃን አለ። ድቅድቅ ጨለማ ከዋጠው ክፍል የአንድ ሰው ድምፅ ይሰማል። ወደ ጨለማው ክፍል ለሚገቡ ሰዎች አንድ እጃቸውን ከፊታቸው ያለ ሰው ትከሻ ላይ አድርገው ወደፊት እንዲራመዱ ትእዛዝ ይሰጣል። ሁሉም ሰው ስልኩን እንዲያጠፋም ቀደም ብሎ ተነግሯል።
እንደ ተባልነው አድርገን ወደ ፊት አንድ ሁለት እያልን ተራምደን ድቅድቅ ጨለማ ከዋጠው ክፍል ውስጥ ገባን። ቀጥሎ እንዴት እንደሚንቀሳቀሱ ማሰብ በጣም የሚያስፈራ ነገር አለው። ምክንያቱም ከድቅድቅ ጨለማ ጋር ከመፋጠጥ ውጪ ምንም የሚታይ አንዳች ነገር የለምና፤ ድምፅ ብቻ ነው የሚሰማው። በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና በጣልያንኛ የሚነጋገሩ ሰዎች ድምፅ በተለያየ ርቀት ይሰማል። በጨለማ ወዲያ ወዲህ እያሉ ሰዎች ቦታ ቦታቸውን እንዲይዙ የሚያደርጉ አስተናጋጆች አሉ። አንደኛው ወደ እኛ መጥቶ ወንበራችንን እንድንይዝ አደረገ። ሁለት ኢትዮጵያዊያን እና አንድ የውጭ ዜጋ ጠረጴዛ ተጋርተን ተቀመጥን። በድቅድቁ ጨለማ ገፅታችን ምን እንደሚመስል ሳንተያይ ተዋወቅን። የትና ምን እንደምንሰራ እንዲሁም ስለ ብዙ ነገሮች እያወራን ደቂቃዎች ሄዱ። አስተናጋጁ የሚጠጣ ነገር እንድናዝ ጠይቆ ይዞልን መጣ። ብርጭቋችንን ከጠጴዛ ላይ በዳበሳ ከማንሳትና በውስጡ ያለውን መጠጥ ለማሽተት ከመሞከር ውጭ ምንም ምርጫ አልነበረንም። አሁንም አሁንም ብርጭቋችንን በዳሰሳ እየፈለግን በማንሳት የቀረበልንን እየተጎነጨን ጨዋታችንን ቀጠልን። • “እናቴ የሞተችው ኤች አይ ቪ እንዳለብኝ ሳትነግረኝ ነው” እዚያ ቦታ ላይ መገኘት ጨለማን እንዲፈሩ፤ አለማየት ሊነገር ከሚችለው በላይ ከባድ እንደሆነ እንዲያስቡ ግድ ይላል። ለቀናት፣ ለዓመታት ብሎም ህይወትን ሙሉ እንዲህ ባለ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ መኖር እጅግ ፈታኝ እንደሆነ አወራን። ይህ የእኔ እጣ ቢሆንስ? የሚል ጥያቄ በእያንዳንዳችን ውስጥ መኖሩ ይሰማል። አስተናጋጁ ዳግም ወደ እኛ መጥቶ ሾርባ አቅርቦልን ዋናው የምግብ ምርጫችንን ጠይቆን ሄደ። በዳበሳ ማንኪያና ሹካ ከሳሃን እያጋጨን ጨለማም ቢሆን እጅና አፍ አይተጣጡም እንደሚባለው በድቅድቁ ጨለማ ሳናይ አጣጥመን ተመገብን። ቀጥሎም ‘ዲዘርት’ ኬክ መጣልን። ምንም እንኳ እየበላን፣ እየጠጣንና እየተጨዋወትን ቢሆንም ጨለማው ጭንቅ የሚያደርግ ነገር አለው። ቀጥሎ ደግሞ የተለያዩ ቀርፃ ቅርፅና ሌሎች ነገሮችን እየመጡልን በመዳሰስ እና በማሽተት ምን እንደሆኑ እንድንለይ ተጠየቅን። በዙሪያችን ያለውን ነገር እንደ ዓይነ ስውር በመስማት፣ በመዳሰስና በማሽተት ለመረዳት መሞከራችንን ቀጠልን። በመጨረሻም በአይነ ስውር አስተናጋጆቻችን እየተመራን ከድቅድቁ ጨለማ ክፍል ወጣን። ይህ ለአንድ ሰዓት ተኩል የሚቆይ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የቀረበ ማዕድ የሚዘጋጀው ዓይናሞች የዓይነ ስውራን ህይወት ምን እንደሚመስል ለደቂቃዎችም ቢሆን እንዲሰማቸው ለማድረግ ታስቦ ነው። አይነ ስውራን እንዴት ይህን ወይም ያን ማድረግ ይችላሉ? ለሚሉ ጥያቄዎችም መልስ ለመስጠትና አጠቃላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው። አቶ ብርሃኑ በላይ የ ‘ቱጌዘር ኢትዮጵያ’ ሥራ አስኪያጅ ናቸው። የሦስት ልጆች አባት ሲሆኑ ልጆቻቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገብተው በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ድርጅቶች በመስራት ላይ ይገኛሉ። • በንቅለ ተከላ ዕይታው የተመለሰለት ኢትዮጵያዊ ታዳጊ አቶ ብርሃኑ ለ40 ዓመታት ያስተማሩ መምህር ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ‘ማዕድ በጨለማ’ ስለ ዓይነ ስውራን ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን መለወጥን ያለመ አንድ የድርጅቱ ተግባር ነው። በጨለማው ማዕድ ላይ ከተካፈሉ በኋላ በሙያዊና በገንዘብ ድጋፍ ከድርጅቱ ጎን የቆሙ በርካቶች እንደሆኑ ይናገራሉ። ነገሩን ለማስፋት በሌሎች አውሮፓ አገራት እንዳሉ ዓይነ ስውራን የሚያስተናግዱባቸው የጨለማ ምግብ ቤት የመክፈት ሃሳብ እንዳላቸውም ይናገራሉ። ድርጅታቸው ሴት ዓይነ ስውራን መጠለያ እንዲያገኙና እንዲማሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ፣ ለዓይነ ስውራን የኮምፒውተር እንዲሁም ዓይነ ስውራን እንዴት መንገድ መሪ በትርን መጠቀም እንዳለባቸውም ስልጠና እንደሚሰጥ አቶ ብርሃኑ ይገልፃሉ። ኮምፒውተር ለዓይነስውራን እንዴት? ሣሙኤል ኃይለማሪያም የአስራ ሁለት ዓመት ታዳጊ ሳለ በመኪና አደጋ ነበር የዓይን ብርሃኑን ያጣው። ከታደምንበት የጨለማው እራት ሁለት ዓይነ ስውራን አስተናጋጆች መካከል አንዱ ነበር። “ሙሉ በሙሉ የእኛን ስሜት ያገኙታል ባይባልም የጨለማው እራት ዓይናሞች የግድ እያንዳንዷን ነገር በእኛ ውስጥ ሆነው እንዲያዩ ያደርጋል። ዓይኔ ከጊዜ በኋላ ስለጠፋ እኔም ራሴን በእነሱ ቦታ አስቀምጣለሁ” ይላል። ራሳቸውን የሚስቱ፣ ከባድ የእራስ ምታት የሚቀሰቀስባቸውና ወደ ድቅድቁ ጨለማ ክፍል መግባት ፈርተው ገና ከበር የሚመለሱም አጋጥመውታል። • “አካል ጉዳተኛ መሆኔ ጥሩ ደረጃ እንድደርስ አድርጎኛል” በሕግና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ሲሆን በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እየሰራ ይገኛል። ላለፉት ስድስት ዓመታት እራቱን የሚያዘጋጀው ‘ቱጌዘር ኢትዮጵያ’ የተሰኘው በጎ አድራጎት ድርጅት ለዓይነ ስውራን የኮምፒውተር ስልጠናዎችን የሚሰጥ ሲሆን ሣሙኤልም ከስልጠናው ተጠቃሚዎች አንዱ ነው። ኮምፒውተር መጠቀም መቻል ለሥራው የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራል። ከስልጠናው በፊት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ ሶፍት ኮፒ ፅሁፎችን ኮምፒውተር ላይ ጭኖ ከማድመጥ በስተቀር በስፋት ኮምፒውተር የመጠቀም ልምድ አልነበረውም። አሁን ግን የለት ተለት ሥራው ከኮምፒውተር ጋር የተቆራኘ እንደሆነ በመግለጽ፤ “ኢንተርኔት እጠቀማለሁ ራሴ ሶፍትዌሮችን እጭናለሁ” ሲል ያስረዳል። ብዙ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩት፤ ውይይቶችና ክርክሮችም የሚደረጉት በማህበራዊ ሚዲያ ነው። የግል ወሬዎች የሚደሩትም እንዲሁ በእነዚህ የበይነ መረብ መድረኮች ላይ ሆኗል። ከዚህ አንፃር ዓይነስውራን የማህበራዊ ሚዲያ ተሳትፎ እንዴት ነው? ለሳሙኤል ያነሳነው ጥያቄ ነበር። “ፌስቡክ አካውንት የከፈትኩት እንዳውም ዩኒቨርሲቲ እያለሁ ነው። ኮሜንት፣ ላይክም ሼርም አደርጋለሁ” በማለት በኮምፒውተር ባይሆንም ቀድሞም በስልክ ኢንተርኔት ይጠቀም እንደነበር አጫወተን። አሁን ደግሞ ቴሌግራም፣ ዋትስአፕና ኢሞም ይጠቀማል። የአውሮፓ እግር ኳስ ውጤቶችን በይበልጥ የሚከታተለው በኢንተርኔት ነው። ኢንተርኔት ቤት ጎራ ብለህ ታውቃለህ? ኤን ቪ ዲ ኤ (NVDA) Non Visual Desktop Access የተሰኘ የኮምፒውተር ገፅን በድምፅ ለማንበብ የሚረዳ ሶፍትዌር በፍላሽ ይዞ ኢንተርኔት ቤት ይሄዳል። ብዙ ጊዜ የኢንተርኔት ባለቤቶቹም ሆኑ ተጠቃሚዎች ወንበር ስቦ ከኮምፒውተር ፊት ቁጭ ሲል ግራ ይጋባሉ። • በዓይነ ስውሯ የተሠራው የሚያይ ሻንጣ “የኢንተርኔት ቤቱ ልጅ አይነ ስውራን ኢንተርኔት እንደሚጠቀሙ ያውቃል። እና ወንበር ሲያሲዘኝ የተጠቃሚው አይን ሁሉ እኔ ላይ እንደሆነ ተሰማኝ። እኔ ኢሜልም እንዲሁ አንዳንድ ገፆችንም ቼክ ሳደርግ የራሳቸው ብር እየቆጠረ ሌሎቹ ተጠቃሚዎች እኔን ያዩ ነበር” እያዩህ እንደሆነ እንዴት አወቅክ? ወይስ ሹክሹክታም ነበር? “ሰው ከጀርባሽ ሲኖር ወይም ሲያይሽ የሚሰማሽ፤ የሚታወቅሽ ነገር አለ። መጨረሻ ላይ ሂሳቤን ከፍዬ ስወጣም የኢንተርኔት ቤቱ ልጅም ነግሮኛል” ድንገተኛ ስራዎች ኖረው ባለበት አካባቢ አቅራቢያ ከሚገኝ ካፍቴሪያ ቁጭ ብሎ ኮምፒውተር ሲከፍት ደግሞ “እንዴት ነው ኮምፒውተር የምትጠቀመው” የሚለው ጥያቄና ግራ መጋባት ይበረታል። ስራ ፍለጋ ለአይነ ስውራን ምን ያህል ከባድ ነው? “ወደ ሰላሳ ቦታዎች አመልክቼ ነው በመጨረሻ የአሁኑን ስራ ያገኘሁት። ለምሳሌ አንድ ቦታ የፅሁፍ ፈተና ጥያቄን ሙሉ በሙሉ ደፍኜ ለቃለ መጠይቅ ተጠርቼ ሄጄ ሲያዩኝ አይነ ስውር ነኝ። ሳላልፍ ቀረሁ። ህግ ያጠና የሚል ማስታወቂያ አውጥተው ስሄድ ላንተ አይሆንም ይሉኛል።” በጥሩ ውጤት መመረቅስ? “በአራት ነጥብ ተመርቀሽ ውጤትሽ ምንም ያህል ያማረ ቢሆን ቀድመው የሚያዩት አካል ጉዳተኛ መሆንሽን ነው” በማለት በተለይም ለአይነ ስውራን በግል ተቋማት መቀጠር የማይታሰብ እንደሆነ ይናገራል። “ጥሎ የማይጥለን መንግሥት ብቻ ይመስለኛል” ይላል።